የሰዉ ሀብት ልማት እና ለዉጥ ትግበራ ዳይሬክቶሬት

ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትከተለውን የሰላም፣የዲሞክራሲ፣የልማትና የመልካም አስተዳደር ፖሊስዎች፣ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች እውን ሊሆኑ የሚችሉት በዋናነት የሰው ሀብት አጠቃቀም ውጤታማነት ሲረጋገጥ ነው፡፡ በመሆኑም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ለመልካም አስተዳደርና ለልማት ጉልህ ሚና መጫወት የሚችል ፐብሊክ ሰርቫንት  መፍጠሩ አስፈላጊ ነው፡፡

የፐብሊክ ሰርቪሱን የሜሪት ሥርዓት እውን በማድረግ ብቃት ላይ የተመሠረተ ፍትሀዊ የሠራተኛ ቅጥርና ምደባ ወዘተ…እንዲኖር በማድረግ የሰዉ ሀብት ሥራ አመራር አገልግሎት አሰጣጥን በተጠያቂነት መርህ ላይ የተመሠረተ ፈጣን፣ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ ልማቱን ለማፋጠን የተንዛዛና ባለጉዳዩን የሚያጉላላ አገልግሎት አሰጣጥን በማስቀረት ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት ሊሰጥ ይገባል፡፡

የሰው ሀብት ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት በመ/ቤቱ ከተዋቀሩት ዳይሬክትሬቶች አንዱ ሲሆን ተቋሙ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት ተልዕኮውን ለመወጣትና ራዕዩን እውን ለማድረግ የሚያስፈልገውን ራሱን ለለውጥ ያዘጋጀ፣ ብቃት ያለው፣ የተገልጋይን ፍላጐት ለማርካትና ውጤት ለማምጣት ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማሟላት ኃላፊነት እና ተልዕኮ ያለው ዳይሬክቶሬት ነው፡፡

ዳይሬክትሬቱ  ኃላፊነቱን ለመወጣት የባለስልጣን መ/ቤቱን ሠራተኞች ተከታታይና ቀጣይነት ያለው የክህሎት ማሳደጊያ ሥልጠና የሚያገኙበትን ፕሮግራሞችን ያዘጋጃል፡፡ለሥልጠናዎቹ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት አፈጻጸማቸውን ተከታትሎ ውጤታማነታቸውን ይገመግማል፡፡

በተቋሙ ውስጥ በመካሄድ ላይ በሚገኙ የለውጥ ሥራ ፖኬጆች፣ በሰው ሀብት ሥራ አመራር ሕጐችና መልካም ሥነ-ምግባር ማስፈን በሚያስችሉ አሠራሮች ላይ የግንዛቤ ማዳበሪያ መድረኮችን ያዘጋጃል፡፡ የሥራ ክፍል ኃላፊዎችንና ሠራተኞችን ውጤታማ የሚያደርጉ ምቹ የሥራ ሁኔታዎችን በመፈጠር የሚከሰቱ ቅሬታዎችንና የዲሲፒሊን ግድፈቶችን ከአድሎአዊነት በጸዳ አሠራር መፍትሄ እንዲያገኙ ክትትል  ያደርጋል፡፡