የውሃ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት

የውሃ ሀብት ዳይሬክቶሬት ዋና ዋና ተግባራት

በውሃ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ከሚከናወኑት ዋና ዋና ተግባራት አንዱ በተፋሰሱ ውስጥ ፍትሃዊ፣ አሳታፊና ዘላቂ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ይህንን ዓላማ ለማሳካት ዳይሬክቶሬቱ በተፋሰሱ የሚገኙትን የውሃ ሀብት ተጠቃሚዎችን በሚጠቀሙት ውሃ መጠንና በሥራ ዘርፋቸው ለይቶ የማደራጀት ሥራ ይሰራል፡፡ እነዚህን የተለዩትን የውሃ ተጠቃሚዎችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ቅንጅታዊ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ሥርዓት የመዘርጋት ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ዳይሬክቶሬቱ በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኘውን የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ አቅም በማጥናት እና የአሁኑንና የወደፊቱን ለተለያዩ ግልጋሎቶች የሚፈለገውን የውሃ ፍላጎት በመተንተን ፍትሃዊና ዘላቂ የውሃ ሀብት ምደባ ሥራ ይሰራል፡፡ በተፋሰሱ ውስጥ ለሚገኙት ባለድርሻ አካላት ስለ ውሃ አጠቃቀም፣ ውሃ አካላት አያያዝና ብክለት ቁጥጥር ላይ ቀጣይነት ያለውን የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራም በዳይሬክቶሬቱ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ለውሃ ተጠቃሚዎች በውሃ የመጠቀም ፈቃድ መስጠት፣ ፈቃድ ማደስ እና የውሃ ታሪፍ ክፍያ ማስከፈል በሥራ ክፍሉ በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

ሌላው በዚህ ሥራ ክፍል እየተገበረ ያለው ተግባር የውሃ አካላት አያያዝና የወንዞች ፍሰት ችግር መከታተል ነው፡፡ የውሃ አካላት ደርቻ ነጻ ክልል ወሰን በጥናት መለየት፣ ይህንን በሚመለከት ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለተፋሰስ ከፍተኛ ምክር ቤት ምክረ ሀሳብ ማቅረብ እና ጸድቆ የሚወጣው ደንብ በተፋሰሱ ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን የመከታተል ሥራ በክፍሉ ይተገበራሉ፡፡ በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኙትን ረግረጋማ መሬቶችን መለየት፣ የተጎዱትን መልሶ ማልማትና መጠበቅ በስራ ክፍሉ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፡፡ በተጨማሪም በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኙ ወንዞች ፍሰት እንድቆራጥና እንድስተጓጎል የሚያደርጉትን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መንስዔዎችን የመለየትና የመቆጣጠር ሥራ እየተገበረ ይገኛል፡፡

በዳይሬክቶሬቱ በትኩረት እየተሰሩ ከሚገኙት ተግባራቶች አንዱ የብክለት ቁጥጥር ማካሄድ ነው፡፡ ከዚህም አንጻር በመተግበር ላይ የሚገኙ ሥራዎች በተፋሰሱ የሚገኙትን የውሃ አካላት የውሃ ጥራት ደረጃ ማወቅና ቁጥጥር ማካሄድ፣ የብከለት ምንጭ መለየት፣   በመስኖ ልማት ሥራዎችና ፕሮጀክቶች አካባቢ ጨዋማነት እንዳይከሰት የከርሰ ምድር ውሃ እንቅስቃሴ መቆጣጠር፣ ከኢንዱስትሪዎችና ከሌሎችም ምንጮች የሚወጣ ፍሳሽ ታክሞ እንዲለቀቅ ለተቋማቶቹ ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣ ስታንዳርዱን በማረጋገጥ የታከመ ፍሳሽ ወደ ውሃ አካላት ለመልቀቅ ፈቃድ መስጠት እና የታከመ ፍሳሽ ወደ ውሃ አካል ለመልቀቅ ፈቃድ ያላቸውን ተጠቃሚዎች ማስከፈል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡