የሴቶች ጉዳይ

ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛት ውስጥ ግማሽ ያህል ቁጥር የሚሸፍኑት ሴቶች ሲሆኑ በህብረተሰቡ ውስጥ በማናቸውም መስክ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት መስፈንና ሴቶችን ማብቃት ለአንድ ሀገር እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡

በዚህም መሰረት የሴቶች ጤና ማሻሻል፣ የትምህርት ተሳትፎአቸውን (ተደራሽነታቸውን) ማሳደግ፣ የኢኮኖሚ እድሎቻቸውን በተለይም የመሬት ማለቤትነትን ማረጋገጥ፣ ስራ የማግኘት ዕድሎቻቸውን ማስፋት፣  የመሪነትና የውሳኔ ሰጪነት ተሳትፎአቸውን ማሳደግ፣ እንዲሁም ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታቸውን በማሻሻል የሴቶችን ድህነትና ለድህነት ተጋላጭነት በመቀነስ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ለማረጋገጥና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት ያስችላል፡፡

የሥርዓተ-ፆታ ጉዳይ ፍትሃዊነትን የተቀዳጀ ለማድረግ መንግሥት የህግ ማዕቀፎችን ከመቅረፁ ጎን ለጎን ያወጣቸውን ህጎች የሚያስፈፅሙና የሚከታተሉ ተቋማትንም አደራጅቷል።

እንዲሁም የሥርዓተ-ፆታ ጉዳይ ከፌደራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ባሉ የመንግስት ተቋማት ውስጥ በሚዘጋጁአቸው ፖሊስዎች የልማት ፕሮግራሞች፣ ፕሮጀክቶች፣ ዕቅድ እና የዕቅድ አፈጻጸም ለማካተትና ተግባራቱን ለመከታተል፣ ለመገምገም፣ እንዲቻልና እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ የተደራጀ ነው።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ባለስልጣን የተቋቋመበት ዋና አላማ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አሰተዳደር ሂደት ፍትሃዊና አሳታፊ በሆነ መንገድ በስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ማበረታታትና መቆጣጠር ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እንዲሰፍን ለማድረግ እንደ አንድ ሴክተር የራሱን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡

እንደሚታወቀው ውሃ ህይወት ላላቸው ፍጥረታት ሁሉ እጅግ በጣም አስፈላጊና መሰረታዊ ነገር ነው፡፡ በተለይም ውሃን ለቤት ውስጥ ለተለያዩ አገልግሎቶች ለምሳሌ ምግብ ለማብሰል፣ ለንፅህና፣ ለጤናና ለመሳሰሉት በቀዳሚነት የሚጠቀሙት ሴቶች ሲሆኑ ወንዶች ደግሞ ለተለያዩ ገቢ ማስገኛ ስራዎች ለምሳሌ ለትልልቅ መስኖዎችና እንስሳት እርባታ በቀዳሚነት ይጠቀሙታል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በአለም አቀፍ ደረጃ ውሃን ለማግኘት፣ ለማስተዳደርም ሆነ ለመጠቀም ሴቶችና ወንዶች ያላቸው ሚና የተለያየ ሲሆን ይሄም የሚሆነው በተዛባ የሥርዓተ-ፆታ አመለካከት፣ ልዩነትና ተፅህኖ ነው፡፡

አለም አቀፉ ሴቶችን የተመለከተ መረጃ (Data from the World’s Women 2010 report) እንደሚያሳየው ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገሮች 63% የገጠር ሴቶች ውሃን ለቤት ውስጥ ፍጆታ የማቅረብ ኃላፊነት ሲኖርባቸው ወንዶች ግን 11% ብቻ ነው፡፡ በከተማ ደግሞ 29% ሴቶች ውሃን ለቤት ውስጥ ፍጆታ የማቅረብ ኃላፊነት ሲኖርባቸው ወንዶች ግን 10% ብቻ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የመጣው ለውጥ እንዳለ ሆኖ አሁንም ድረስ በሁሉም ታዳጊ ሀገራት ውሃን ለቤት ውስጥ አገልግሎት ከሩቅም ሆነ ከአቅራቢያቸው የማቅረብ ኃላፊነትና ጫና በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ ነው፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትላቸው ተፅህኖዎች አንዱ የውሃ እጥረት መከሰትና የጎርፍ አደጋዎች ሲሆኑ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከዚህ ጋር ተያይዞ ሴቶችና ህፃናት በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ናቸው፡፡ በዚህም ምክኒያት ሴቶችና ህፃናት ትምህርታቸውን ስለሚያቋርጡ በታዳጊ ሀገራት ላይ ያለው ድህነት፣ ብሎም የሴቶችና የወንዶች እኩልነት አለመረጋገጥ እየተባባሰ ሊመጣ ይችላል፡፡ በመሆኑም ይህንን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ሀገራችንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሂደት አሳታፊ፣ ፍትሐዊና ዘላቂነት/ቀጣይነት/ ባለው መንገድ እንዲመራ የማስተዳደርና የመምራት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ እንደሚታወቀው ከ4ቱ መርሆዎች አንዱ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሴቶችን ማህከል ያደረገ መሆን እንዳለበትና በውሃ አቅርቦት፣ አስተዳደርና አያያዝ ሂደት ላይ የሴቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን መረዳትና ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡

የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ባለስልጣንም በተፋሰሱ ውስጥ ሴቶች በተለያዩ ዘርፎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ብሎም እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ትኩረት ሰጥቶ እየተገበረ ይገኛል፡፡