ስለእኛ

የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ባለስልጣን፡-

የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ባለስልጣን በተፋሰሱ ውስጥ የሚስተዋሉትን የውሃ ሀብት ችግሮች በአዋጅ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሠረት ለመፍታት በሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 253/2003 የተቋቋመ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ነው፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱ ፍትሀዊ፣ አሳታፊና ዘላቂ በሆነ መንገድ የውሃ ሀብት አጠቃቀምን የሚያረጋግጡ ተግባራትን በማከናወን በተፋሰሱ ውስጥ ያሉትን ሀይቆች፣ ወንዞች፣  እንዲሁም  ሌሎች የውሃ አካላትን የማይጎዳ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ሥርዓት በመዘርጋት የውሃ ሀብቱን መጠንና ጥራት ዘላቂነት ያረጋግጣል፡፡

የባለስልጣን መ/ቤቱ ዓላማ፡-

የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሂደት ፍትሃዊና አሳታፊ በሆነ መንገድ በስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ማበረታታትና መቆጣጣር ነው፡፡

የባለስልጣን መ/ቤቱ ተልዕኮ፡-

በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረተ፣ አግባብነት ያላቸውን አካላት ያሳተፈ፣ የተፋሰሱን ስነ- ምህዳር ሚዛን የጠበቀ፣ ዘላቂነት ያለውና ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሥርዓት በተፋሰሱ ውስጥ ማስፈንና ተግባራዊ ማድረግ፣

የባለስልጣን መ/ቤቱ ራዕይ፡-

የተቀናጀ ሁሉን አቀፍ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሥርዓት የሰፈነበትና የተፋሰሱን ስነ-ምህዳር ሚዛን የጠበቀ ሞዴል ተፋሰስ ሆኖ ማየት፣

እሴቶች

 • አዲስ ሃሳብና ፈጠራ
 • ታማኝነት
 • እኩልነትና ተጠቃሚነት
 • ቅድሚያ ለጥራት
 • ፅናትና ቁጭት
 • አካባቢ ጥበቃና ዘላቂ ልማ
 • ሁል ጊዜ መማር
 • የቡድን ሥራ
 • ሙስናንና ብልሹ አሠራርን መፀየፍ

ባለስልጣኑ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ያሉት ሲሆን እነርሱም፡-

 1. የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በተፋሰሱ ውስጥ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚረዱ የፓሊሲ ሀሳቦችን በማመንጨት ለከፍተኛ ምክር ቤቱ ያቀርባል፤ ሲፈቀድም ተግባራዊነቱን ይከታተላል፤
 2. በተፋሰሱ ውስጥ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሂደትን ለማስፈፀም የሚረዱ ተግባራትን ያከናውናል፤ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤
 3. በተፋሰሱ ውስጥ ከውሃ ጋር የተገናኙ ፕሮጀክቶች፣ ተግባራትና መስተጋብሮች በይዘታቸው፤ በጊዜ ሠሌዳቸው፣ በውጤታቸውና በአመራራቸው ከተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሂደቶች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ያረጋግጣል፤
 4. የተፋሰስ ዕቅድ በማዘጋጀት ለከፍተኛ ምክር ቤቱ ያቀርባል፤ ሲፈቀድም ተግባራዊነቱን ይከታተላል፤
 5. ለክልሎች በሕግ የተሰጠው ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ በተፋሰሱ ውስጥ በውሃ ለመጠቀምና ውሃ ነክ ሥራዎች ለመሥራት የሚያስችል ፈቃድ በአዋጅ አንቀጽ ፲፭ መሠረት ይሰጣል፤ በፈቃድ የተመለከቱ ሁኔታዎች መከበራቸውን ያረጋግጣል፤
 6. በተፋሰሱ ሚገኘውን የውሃ ሀብት በተገቢው ሁኔታ ለማቀድ፤ ለማስተዳደርና ለማንቀሳቀስ የሚጠቅሙ መረጃዎችን ይሰበስባል፤ ያጠናክራል፤ ይተነትናል፤ ያሰራጫል፤
 7. የተፋሰሱን ውሃ ሀብት ስትራቴጂክ ዕቅድና የውሃ አስተዳደር ተግባራትን ለመምራትና ለመደገፍ እንዲያስችል የተፋሰስ ሞዴል ያዘጋጃል፤ ይጠቀማል፤
 8. የውሃ ምደባና አጠቃቀምን ስለሚመለከቱ አለመግባባቶች አፈታት ለከፍተኛ ምክር ቤቱና ለሚኒስቴሩ የምክርና የቴክኒክ ድጋፍ ይሰጣል፤
 9. አግባብ ባላቸው አካላት መካከል ውጤታማ የግንኙነት መድረክ በመፍጠር ቀጣይነት ባለው ሁኔታ እንዲካሄድ ያደርጋል፤
 10. ከተጠቃሚዎች የውሃ ክፍያ ይሰበስባል፤
 11. ከሌሎች አገሮች ጋር ድንበር ዘለል ወንዞችን በሚመለከት ለመወያየት አግባብ ላለው አካል በከፍተኛ ምክር ቤቱ መመሪያ መሠረት አስፈላጊ እርምጃዎችን አዘጋጅቶ ያቀርባል፤
 12. ተግባራትን ለማከናወን የሚረዱ ጥናቶችን፤ ቅኝቶችንና ምርምሮችን ያካሂዳል፤
 13. በመስኖ ልማት ሥራዎችና ፕሮጀክቶች አካባቢ ጨዋማነት እንዳይከሰት የከርሰ ምድር ውሃ እንቅስቃሴን በመቆጣጠር እርምጃዎችን እንዲወሰዱ ያደርጋል፤
 14. የወንዝ አቅጣጫ አመራር ሥራ ይሠራል፤
 15. የንብረት ባለቤት ይሆናል፣ ውል ይዋዋላል፣ በራሱ ስም ይከሳል፣ ይከሰሳል፤
 16. ዓላማውን ለማስፈፀም የሚያስፈልጉ ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል::